 |
|  |
|
|
|
|
|
|
የኃላፊው መልዕክት
ዓለም በለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች፣ አገራችንም የዓለም የለውጥ እንቅስቃሴ አካል እንደመሆኗ መጠን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ለማሳካት በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የዕድገት ጐዳና በመጓዝ መንግስት ድህነትን ከአገሪቱ በማጥፋት ህዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ደረጃ ለማድረስ ያላሳለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል:: ይህ ግብ ሊሳካ የሚችለው ሁሉም ዜጋ አገሪቷ የነደፈቻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በሚገባ ከመገንዘብ አልፎ ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የየራሱ ድርሻ መወጣት ሲችል ነው::
በመሆኑም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት የሀገሪቱ ህገመንግስት፣ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በየጊዜው የሚወጡ ህጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እነዚህንም ለማስፈፀም የሚወጡ ወቅታዊ ዕቅዶች ለመተግበር በህግ ተለይተው በተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መሠረት የዜጐች ንብረት የማፍራት፣ የመጠቀም፣ ህጋዊ በሆነ መንገድ ለሌሎች የማስተላለፍ ህገ መንግስታዊ መብት በጥብቅ እንዲከበር ጠንክሮ ይሰራል:: በዚህም በየትኛውም ደረጃ ባሉ የፍትህ አካላትና በሀገር ውስጥና በውጭ አገር ጭምር በእኩል ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውና እምነት የሚጣልባቸው ተጣርተው የተረጋገጡና የተመዘገቡ ህጋዊ ሰነዶች በማመንጨት የፍትህ ሥርዓቱን በማገዝና ኢንቨስትመንቱን በማሳለጥ እስከአሁን ሲጫወተው የነበረው ሚናና ሲያበረክተው የነበረው አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያምናል::
ተቋሙ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ባለው ፈጣን፣ ጥራት ያለው፣ ተደራሽና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እስከአሁን በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተገልጋዮችና ከሌሎች ገለልተኛ አካላት በርካታ ሽልማቶችና የዕውቅና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውለታል:: እነዚህ ሽልማቶች አመራሩና ሠራተኛው ለበለጠ ውጤት እንዲነሳሳ የሚያበረታቱት እንጂ የሚያዘናጉት ወይም የሚያዘናጉት አይደሉም:: በመሆኑም የጽ/ቤቱ ማኔጅመንትና ሠራተኛ አሁን ተቋሙ እያከናወነ ያለው የመሠረታዊ የአሠራር ሂደት ለውጥ (BPR) እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ የውጤት ተኮር የምዘና ስርዓት (BSC) ተግባራዊ ያደርጋል:: ከአሁኑ በተሻለ ተገልጋዩን የሚያረካ ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በበቂ ባለሙያዎች የታገዘ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያለው፣ ፈጣንና በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ብቁ ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ሞዴል ተቋም እንዲሆን በማድረግ አገራችን ለነደፈችው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊነት የበኩላችንን ድርሻ እንደምንወጣ በድጋሚ ቃል የምንገባበት ወቅት እንደሆነ አምነን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን::
ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምትገናኙ ባለድርሻ አካላትና የተከበራችሁ ተገልጋዮቻችንም የተቋሙ ራዕይ እንዲሳካና የአግልግሎት አሰጣጡም የተሻሻለና የበቃ እንዲሆን የየበኩላችሁን ድጋፍና እገዛ እንዳይለየን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ይርጋ ታደሰ
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ኃላፊ
“ምንጊዜም በማያቋርጥ የለውጥ ማእበል ደንበኞቻችን ለማርካት ተግተን እንሰራለን!!!”
|
|

|
|
|
|
|
|
 |
|  |
|